ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመውጫ ፈተና ዙሪያ ውይይት ተደርጓል ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የመውጫ ፈተና የሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱና ዋነኛው የጋራ መወዳደሪያ መስፈርት ነው፡፡
የመውጫ ፈተናን ውጤት መሰረት በማድረግም የግልና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እርስ በርሳቸው እንደሚወዳደሩ ሚኒስትር ደኤታው አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ጥሩ ውጤት ሊገኝ የሚችለው ጥሩ ሂደት ሲኖር በመሆኑ ተቋማቱ ተማሪዎች ለውጤት እንዲበቁ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ዶ/ር ፋንታ አስገንዝበዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው በመውጫ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደሩ ላይ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻዎች እንደሚሳተፉበትና በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በማእከል እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ለምረቃ መብቃትና የትምህርት ማስረጃዎቻቸውንም መውሰድ የሚችሉት የመውጫ ፈተናውን ካለፉ በኋለ መሆኑን ጠቁመው በፈተናው ያላለፉ ተማሪዎችም ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ደግመው መፈተን የሚችሉበት አሰራር እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመውጫ ፈተና ዙሪያ ለሚያደርጉት ዝግጅትም የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል፡፡

የግል ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሞላ ጸጋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የትምህርት ሚኒስቴር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየሰጠ ላለው የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ፣ የመምህራን ትምህርት እድልና ሌሎችም ድጋፎች አመስግነው በ3ኛ ዲግሪ እየተሰጠ ያለው የትምህርት እድል ከፍ እንዲል ጠይቀዋል፡፡
በግልና በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ የህግ አተገባበር ልዩነቶች እንዳሉ ጠቅሰው ይህም እንዲስተካከል ዶ/ር ሞላ አመልክተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ስራዎች እና የመውጫ ፈተና ምንነትና ዝርዝር አተገባበር የተመለከቱ ጽሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ምንጭ:- ትምህርት ሚኒስቴር ፌስቡክ ፔጅ

