ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶች እና አመራሮች ጋር በዘርፉ እየታዩ ያሉ ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው በሳሪም ኢንተርናሽናል ሆቴል የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እንዳሉት፤ በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ዙሪያ ከፍተኛ ችግሮች እንዲፈጠሩና ሂደቱ ወደ ኋላ እንዲጎተት ያደረጉትን ምክንያቶች በመለየትና በማጥራት ለህብረተሰቡ፣ለመንግስት እና ለሚዲያ አካላት ተደራሽ እንዲሆና ግልጽነት እንዲፈጠር በማድረግ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡

በዘርፉ ያሉት ችግሮች ለህዝብ ይፋ በመደረጉ መንግስትም ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረጉን ገልጸው፤ለአብነትም በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት 3 ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እንዲሾሙ መደረጉ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቦርድ ሥራ አመራር እንዲኖሩት መደረጉ፣ ተቋሙ ከኤጀንሲ ወደ ባለሥልጣን እንዲያድግ መደረጉ እና አደረጃጀቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ እንዲደራጅ መደረጉ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች መንግስት ለተቋሙ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመለክቱ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች ስፋትና ጥልቀት አንጻር መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ችግሩን ከምንጩ ለይቶ ማድረቅ የማይቻል በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ ፣ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በዘርፉ የሚታዩ የመመሪያ ጥሰቶችን ሲገልጹ ዋና ዳይሬክተሩ ባልተፈቀደ ካምፓስ እና ቦታ ማስተማር፣ ሲኦሲ ሌላ ጊዜ ታሟላላችሁ በሚል መስፈርት ያላሟሉ ተመዝጋቢዎችን መቀበል፣ የእውቅና ፈቃድ ባገኙበት ህንጻ አለመገኘት እና እውቅና ፈቃድ ለማግኘት ብቻ ህንጻ የሚከራዩና ኪራዩ በሂደት ለሌላ ህገወጥ ተግባር ውስጥ የሚገቡ እና በመሳሰሉት የመመሪያ ጥሰቶች ወደ 373 ካምፓሶች የእርምት እርምጃ ወስደን ለህብረተሰቡ በሚዲያ ተቋማት ይፋ መደረጉ እና ይህን ያህል ቁጥር የመመሪያ ጥሰቱ በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አስደንጋጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

ችግሩን ባለበት ለማስቆም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማኅበራቸው መደራጀት እንዲደራጁ፣ ሲደራጁ ተደማጭነታቸው እንደሚጨምር እና ህገ-ወጥነቱንም ማስቆም እንደሚቻል የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ምክርና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ ህገወጥ ስራ የሰሩ ተቋማት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በወንጀልና በፍትሐብሂር ይጠየቁ የሚለው ሐሳብ ሆኗል፡፡ እኛ በዚህ መልኩ ተጠያቂ ባለማድረጋችን ጥያቄው ወደኛ እየመጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የኢንስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና ቁጥጥር ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነ በበኩላቸው ተቋሙ ስለተቋቋመበት ዓላማ፣ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ስለተሰሩ ስራዎች ውጤቶች፣ ስለአጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
በባለስልጣኑ የፈቃድ አሰጣጥ እና ጥራት ኦዲት ም/ዋና ዳይሬክተር ተደራሽነትና ጥራትን ያማከለ አሰራር መዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በባለሥልጣኑ የእውቅናና ስታንዳርዳይዜሽን ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዱንካና ኑጉሳ በበኩላቸው ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እና አሁን ያለበት አቋም ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሞላ ጸጋዬ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበራቸው በምንም መልኩ ከህገወጥ ተቋማት ጎን እንደ ማይቆም፣ባለሥልጣኑ በህገወጥ ተቋማት እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፣ ተቋማት የሚፈጽሙትን የህግ ጥሰት አምነው ባለማስተካከላቸው ባለሥልጣኑ ሰርቶም እንዳልተሰራ እተገለጸ በመሆኑ እኛ የግል ተቋማት በፍጥነት ከዚህ ልንታረም ይገባል ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡