===== ====== ======
-ጥናት ካካሄደባቸው 10 ሺ የትምህርት ማስረጃዎች 505ቱ ሀሰተኛ ናቸው
አዲስ አበባ፡- የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በ2014 በጀት አመት የስነ ስርዓት ጥሰት በፈጸሙ ከ350 በላይ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ ከአረጋገጣቸው 10 ሺ የትምህርት ማስረጃዎች 505 ቱ ሀሰተኛ ናቸው ብሏል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በ2014 በጀት አመት ከየትኛውም በጀት አመት የበለጠ የትምህርት ጥራትን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን የማጽዳት ስራ ተከናውኗል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ ገምግሞ አቅጣጫ ካስቀመጠ ጊዜ ጀምሮ ከ350 በላይ በሚሆኑ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡
መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸው ካሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ውስጥ ሕገ ወጥ የትምህርት ተቋማትን መቆጣጠር አንዱ ተግባር ነው ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ አሁን ላይ የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ትርፍን ብቻ አላማ ያደረጉ ሕገ ወጥ የግል የትምህርት ተቋማት መስፋፋት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋምና ፕሮግራም መዝጋት አማራጭ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የእውቅና ፈቃድ ሳይሰጣቸው በትውልድ ህይወት የሚነግዱ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡
እንደ ዶክተር አንዷለም ገለጻ፤ በርካታ ዜጎች እውቅና በሌለው የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገንዘባቸውን ከፍለው ከተማሩ በኋላ ባለስልጣኑ ማረጋገጫ ሲሰራላቸው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሆንባቸው ለተመሰቃቀለ ህይወት እየተዳረጉ ነው፡፡ በተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ በ355 የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ከፕሮግራም መዝጋት እስከ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ እስከ መዝጋት የደረሰ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ለዚህም መገናኛ ብዙሃን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ስራ በበጀት አመቱ በትኩረት ከተሰራባቸው መካከል መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር አንዷለም፤ በዘርፉ የጤና ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን ለሚቀጥሯቸው ሰራተኞች ቅጥር ከመፈጸማቸው በፊት የትምህርት ማስረጃቸው በባለስልጣኑ እንዲረጋገጥ የሚያደርጉበት አግባብ ለህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃ ቁጥጥር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ዕድገትና ቅጥር ሲያከናውኑም በሙሉ ሳያስፈትሹ እንደማያከናውኑ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ የትምህርት ማስረጃ ሲረጋገጥ በቀጣሪ መስሪያ ቤቶች ተገደው የሚመጡ አካላትን የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና ከውጭ አገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃን አቻ ግምት በመስጠት በሁለት መልኩ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ የማረጋገጥ ስራ የሚጀምረው ከአገር አቀፍ ፈተናዎች እንደሆነና በወቅቱ ከነበረው የመቁረጫ ነጥብ በመጀመር እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃ ተፈትሾ እስከ ዲፕሎማና ዲግሪ እንደሚረጋገጥም ጠቁመዋል፡፡
በ2014 በጀት አመት የጤና ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽንን ሳያካትት ተገደው ከመጡ ከ10 ሺ በላይ የትምህርት ማስረጃዎችን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ዶክተር አንዷለም፤ ከተረጋገጡት የትምህርት ማስረጃዎች 505 የሚሆኑት ትክክለኛ ያልሆኑ የትምህርት ማስረጃዎች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
ፈቃድ ሳያገኙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዱ ያሉ ትውልድን እያቀጨጩ የሚገኙ ሕገ ወጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ሂደት ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግም ዶክተር አንዷለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ
ምንጭ:- የኢፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ፌስ ቡክ ገፅ