=========== ==========
የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበር የቦርድ አባላት ከኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም በባለሥልጣኑ መሰብቢያ አዳራሽ ባደረጉት ውይይት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉ እንደሚገባና አዲስ የተቋቋመው ቦርድም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቦርዱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ገልጹ፡፡

በባለሥልጣኑ የተጀመረው አዲስ የለውጥ ስራ ጥሩ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ የቦርድ አባላት ህገወጥ ተቋማት ተለይተው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እና ጥሩ ስራ እየሰሩ ያሉና የተጣላባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ ያሉ ተቋማት ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡የትምህርትን ጥራት የማረጋገጡ ስራ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት ተጠናክሮ ሊቀጥልና የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎች ቀጣይነት ያለው እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

የትምህርትና ስልጣና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ ህገወጥ ስራ በሚሰሩ ከተፈቀደላቸው የተማሪ ቁጥር በላይ መሟላት የሚገባቸውን ሳያሟሉና ለባለስልጣኑ ሳያሳውቁ ተማሪ ተቀብለው በሚያስተምሩና በሚያስመርቁ፣ ህግን በሚጥሱ፣ ለትምህርት ጥራት ትኩረት በማይሰጡ፣ ተገቢውን የከፍተኛ ትምህርት ቅበላ መስፈርት ያላሟሉ ተማሪዎችን ተቀብለው በሚያስተምሩና በሚያስመርቁ እና ፈቃድ ባልተሰጣቸው የትምህርት መስኮችተማሪዎችን ተቀብለው በሚያስተምሩና በሚያስመርቁ ተቋማት ላይ ባለሥልጣኑ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የኢንስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ተቋማት ህግን አክብረው ከሰሩ፣ ሁሉም የሚጠበቅበትን በአግባቡ መወጣት ከቻለ፣ ችግሮች እንዲሻሻሉ ጠንክረን ከሰራን ከትምህርት ጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር መፍታት የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእውቅናና ስታንዳርዳይዜሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ በበኩላቸው የሙያ ማህበራት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል፡፡ የሙያ ማኅበራት እራሳቸውን ካጠናከሩ የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል ትልቅ አስተዋጾ ሊያበረክቱ የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህዳር 20/2015 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ